ያልተሳካው የእነ ጃዋር የጥፋት ድግስ!!

የኢሬቻ በዓልን ባህላዊ አከባበር ጠብቆ ለማክበር የኦሮሞ ህዝብ፣ አባገዳዎችና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሰፊ ቅድመ ዝግጅት ቢያደርጉም በሁከት ፈጣሪ ኃይሎች ምክንያት መስተጓጎሉ የሚታወስ ነው፡፡ በዓሉን ለማወክ አስቀድመው የተዘጋጁ ኃይሎች ባስነሱት ሁከት በተፈጠረ ግርግር በመረጋገጥ የሰው ህይወት መጥፋቱም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

በሁከትና ብጥብጥ ጀርባ በአቶ ጃዋር መሀመድ የሚመራው የጥፋትና ሀገር የመበታተን አጀንዳ ያለው ኃይል መኖሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የጥፋት ኃይሉ ከሁከቱና ግርግሩ በስተጀርባ መኖሩንና አመራር ይሰጥ እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎችን አንድ በአንድ እንመለከታለን፡፡ የጥፋት ሀይሉ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ብቻ አላበቃም፡፡

ሁከቱን በማጉላትና በመንግስት ኃይሎች ላይ ለማላከክ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ነበር፡፡ የጥፋት ኃይሉ ተልእኮ የበዓል ስነ-ስርዓት ላይ ታድመው የዘገቡ አለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋዜጠኞችንም እስከ መዝለፍ የደረሰ ነው፡፡ በጃዋር የሚመራው የጥፋቱ ኃይል የውጭ ሚዲያዎችን ዘገባና ራሱ ዘጋቢዎችን ወይም የውጭ ሚዲያ ጋዜጠኞችን እንዴት ያጥላላ እንደነበር በማስረጃ በማስደገፍ ለማሳየት እንሞክራለን፡፡

በኦሮሞ ህዝብ ልዩ የባህል መገለጫ በሆነው የኢሬቻ በዓል ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ተውጣጥተው እንዲመጡ ያደረጋቸው የጥፋት ሃይሎች መታወቂያ ሳይዙ ወደ በአሉ እንዲገቡ ጃዋር ፖስት በሚያደርጋቸው ጽሁፎቹ በተከታታይ ሲያስጠንቅቅ ነበር፤ ይህም ሁከቱ ታቅዶ ይከናወን እንደነበር አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይህም በአሉ ላይ ሁከቱን እንዲመሩ ትእዛዝ የተሰጣቸው ኃይሎች የሁከት ፈጣሪዎች ማንነት እንዳይታወቅ ለማድረግ እንደነበር ብዙዎቹ ይስማሙበታል፡፡

የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት የማይጥማቸው ኃይሎች ጋር ተቀናጅተው ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ያነገቡት እነ ጃዋር ለሁከት ተግባራቸው ያግዘናል ብለው ያሰቡት ኃይል ከሌሎች ክልሎች ጭምር በማስመጣት ኢሬቻ በዓል ላይ እንዲሳተፉ አድርገዋል፡፡ በጃዋር የሚመራው ኃይል በዓሉ ላይ የተገኙ የጥፋት ኃይሉ ወኪሎች ከሌሎች ክልሎች የመጡትን ተልዕኮ አስፈፃሚዎች ቃለ ምልልስ እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ ይወተውት ነበር፡፡

 

የውጭ ኃይሎች ተልዕኮ ለማስፈፀም በጃዋር የሚመራው የጥፋት ኃይል ያነሳው ሁከትና ግርግር የተፈለገውን ውጤት ማምጣት ባለመቻሉ የተፈጠረውን ጉዳት ማጉላትና በፀጥታ ኃይሉ ለማላከክ ያልተፈነቀለ ድንጋይ የለም፡፡ የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ኃይል የኢሬቻ በዓል ክብርና ሞገስ እንዳይጐደፍ ሁከት ፈጣሪዎችን መታገስ ከሚገባዉ በላይ መታገሱ ከስፍራው የወጡ ቪዲዮዎች በግልፅ ያሳያሉ፡፡ አልተሳካም እንጂ በሁከቱና ግርግሩ የተጐዱና ለህልፈት የተዳረጉ ሰዎችን በፀጥታ ኃይል ተተኩሶ የተገደሉ ለማስመሰል ያላደረጉት ጥረት የለም፡፡

የጥፋት ኃይሉ በስፍራው ተገኝተው ትክክለኛውንና እውነተኛውን እማኝነት ይሰጡ የነበሩ ግለሰቦችን ለማሸማቀቅ እና ለማጥላላት ጊዜ አልፈጀበትም፡፡

የማጥላላትና የማሸማቀቅ ዘመቻው በዜጐቻችን ላይ ብቻ የታጠረ አልነበረም፡፡ ሁነቱን ለመዘገብ በቢሾፍቱ የተገኙ አለም አቀፍ የሚዲያ አውታሮችንና ጋዜጠኞቻቸው ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡ የመንግስት ጸጥታ ሀይሎች በህዝቡ ላይ ምንም ዓይነት ጥይት በህዝቡ ላይ አለመተኮሳቸውንና ጉዳዩ የደረሰው በመረጋገጥ (Stampede) እንዲሁም ሁከት ፈጣሪዎቹ በፀጥታ ኃይሎች ላይ ድንጋይ፣ ጠርሙስና የመሳሰሉ ቁሳቁችን ቢወረውሩም የፀጥታ ኃይሎች ግን በከፍተኛ ትእግስት ማሳለፋቸውን እማኝነታቸውን በመግለፃቸው የስድብ ናዳ ወርዶባቸዋል፡፡ ለአብነት የጥፋት ኃይሎች መሪ ጃዋር መሀመድ በአለም አቀፍ ዜና አውታር ጋዜጠኞች ላይ የሰነዘረውን ስድብና ዘለፋ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

" በውጭ ጋዜጠኞች በጣም ተናድጃለሁ፡፡ ከ30 በላይ ጋዜጠኞች በስፍራው ይገኛሉ፡፡ አንዳቸውም የኢትዮጵያ መንግስት እያደረሰ ያለውን ጥፋት አይዘግቡም፡፡ ለምን? የሆቴልና የጉዞ ወጪ በመንግስት ተሸፍኖላቸው ይሆን?

ቢቢሲዎች ማፈሪያ ናችሁ እንዴት ዓይነት አናዳጅ ሪፖርት ነው ያቀረባችሁት፡፡ የትኛው ሪፖርተራችሁ ነው ይህን የዘገበው፡፡

 

ቢቢሲዎች ምን ነክቶአችሁ ነው፡፡ ታዳሚዎች በፖሊስ ላይ ድንጋይ ወረወሩ የምትሉት፡፡ ሄሊኮኘተሮች አስለቃሽ ጋዝና ጥይት ሲተኩሱ የት ነበራችሁ?

ደግሞ ወደ ዋሺንግተን ፖስት ስድቡን ያዞራል

" ዋሺንግተን ፖስቶች ይህን የደደብ ሪፖርታችሁን አስተካክሉ፡፡ ዋናው ምክንያት የሰዎች መረጋገጥ ሳይሆን ከሄሊኮኘተር የተተኮሰው ጥይትና አስለቃሽ ጋዝ ነው፡፡ ማረጋገጥ ከፈለጋችሁ የውጭ ጋዜጠኞችንና ዲኘሎማቶችን ጠይቁ፡፡ እውነቱን ለመግለጽ ከፈለጉ ማለት ነው፡፡

በጃዋር የሚመራው የጥፋት ኃይል ሀገር ለማተራመስ የማይፈነቅለው ድንጋይ ላለመኖሩ ሌላ ማሳያ መቀመጫውን አሜሪካ ኒውዮርክ ባደረገው ብሉምበርግ የተሰኘው አለም አቀፍ የዜና የሚዲያ ሪፖርተር ከሆነው ዊልያም ዴቨንሰን ጋር በጃዋር ፌስ ቡክ ገጽ ያካሄዱት ክርክር ነው፡፡ በዚሁ በፌስቡክ ምልልስ የብሉምበርጉ ጋዜጠኛ ዊልያም ዴቨንሰን ጃዋር በሃሰት ያሰፈረውን "በሄሊኮኘተር በታገዘ ጥይት ታዳሚዎች ተደብድበዋል" ያለውን መሰረተ ቢስ ወሬ በእውነተኛ ማስረጃ አስደግፎ ይሞግታል፡፡

የጽሑፍ ምልልሱ እንደሚከተለው ቀርቢል፡፡

ጃዋር ፡- " በአራት ሚሊዮን በዓል በማክበር ላይ ያሉ ያልታጠቁ ሲቪሎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች በምድርና በሰማይ እየተኮሱ ይገኛሉ፡፡

ዊሊያም ዴቪንሰን ፡- አቶ ጃዋር ሄሊኮኘተር በታዳሚዎቹ ላይ ሲተኩሱ የዝግጅቱ ቪአይፒ ታዳሚ እንደመሆኔ ፈጽሞ አላየሁም

ዊሊያም ዴቪንሰን ፤ እንደ ጋዜጠኛ በአይኔ ያየሁትን ነገር እንደ መረጃ መጠቀም ፍትኃዊ ውሳኔ ነው ብዬ አምናለው፡፡ የኢሬቻ በዓል አከባበር ስነ-ስርዓት በአመዛኙ ወደ ተቃውሞ መድረክ መቀየሩንና ተቃውሞ አድራጊዎቹ ዋናውን መድረክ እስከመቆጣጠር መድረሳቸውን እኔም አይቻለው፤ በተጨማሪም ከቪዲዮዎች ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

የበዓሉ አከባበርም ከአዘጋጆቹ ቁጥጥር ውጭ ስለመውጣቱ መረዳት ብዙም አያዳግትም፡፡ የበዓሉ ታዳሚዎች በሄሊኮፕተርም ጭምር በታገዘ ጥይት ተተኩሶባቸው ተገድለዋል የሚሉ አካላት ካሉ ምንም አይነት በቂ ማስረጃ የማይቀርብበት ነው፡፡ በመሆኑም አብዛኛዎቹ ሰዎች እርስ በእርስ በመገፋፋትና በመረጋገጥ ለህልፈት ስለመብቃታቸው አንዱ እማኝ መሆን እችላለሁ፡፡

ይገባል በጃዋር የሚመራው ኃይልን ጨምሮ የውጭ ኃይሎች ተልዕኮ ተቀብለው ሀገር የማተራመስ ተግባር የሚያከናውኑ ኃይሎች ግባቸውን ለማሳካት ምንም ዓይነት ነገር ከማድረግ ስለማይቦዝኑ እንደ አይን ብሌናችን የምንሳሳለትን  ሀገራችንን ለመጠበቅ ከምንም ጊዜ በላይ ትኩረት የምናደርግበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡