ኢትዮጵያ በጎብኝዎች ተመራጭ ሀገር!

ኢትዮጵያ በአውሮፓ የቱሪዝምና የንግድ ምክር ቤት የ2015 ምርጥ የቱሪስት መዳረሻና የባህል ተመራጭ ሀገር በሚል በ2007 እውቅና አግኝታለች፡፡

 የአውሮፓ የቱሪዝም እና ንግድ ምክር ቤት ደግሞ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ከ31 ሀገራት ጋር ተወዳድራ አሸናፊ እንደሆነች ይፋ አድርጓል፡፡ ምክር ቤቱ ለውጤቱ መገኘት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ላላቸው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ግንባር ቀደም የአለም ቱሪዝም መሪ በማለት ዕውቅና እና ሽልማት ሰጥቷል።

 

 በውድድሩ "ኢትዮጵያ በፈጣሪ የተመረጠች ምድር፤ ፍፁማዊት የባህል ቅርሶች መገኛ" "Ethiopia the perfect cultural destination፤ the land chosen by GOD" በሚል ርእስ በምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር አንቶን ካራጋም እጩ ሆና ቀርባ ነው ያሸነፈችው።

 ባህሎቿ፣ በአለም ቅርስነት የተመዘገቡት 24 ቅርሶቿ ፣ ሰላማዊ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሁም ዘርፉ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረጉ ካስመረጧት መስፈርቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

 እነዚህን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ የቱሪዝም ሀብቶች ለአለም ማስተዋወቅ ወቅቱ የሚጠይቀው ነው።

 ለዚህም ይመስላል ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ አመታት ስትታወቅበት የነበረውን ገፅታ የሚቀይር አዲስ የቱሪዝም መለያ ይፋ አድርጋ ወደ ስራ የገባችው።

 አዲሱ የኢትዮጵያ ቱሪዝም መለያ

 "ኢትዮጵያ የሁሉ መገኛ ምድር'' /Ethiopia LAND OF ORIGINS / የተሰኘው አዲሱ ልዩ መለያ አገሪቱ ያላትን ተፈጥሯዊ፣ ሰው ሰራሽ ቅርሶቿንና ታሪኮቿን ለማስተዋወቅ ይረዳል። ኢትዮጵያን በዓለም ቱሪዝም ገበያ ተፎካካሪ እንድትሆን የሚያስተዋውቅ እና ለጎበኝዎቿ መተማመኛ የሆነው አዲስ መለያ /ብራንድ/ ሐምሌ 7 ቀን 2008 ዓ.ም ይፋ ሆነ፡፡

 

 የባህልና ቱሪዝም መረጃ እንደሚገልፀው የአዲሱ ብራንድ መዘጋጀት በዋናነት ኢትዮጵያ ላለፉት ግማሽ ምዕተ ዓመታት "ኢትዮጵያ የ13 ወር ፀጋ" በሚል መጠሪያ ስትጠቀምበት የቆየች ብትሆንም ኢትዮጵያ በቱሪዝም መሰህቦቿ አሁን የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃ የሚያሳይ አለመሆኑንና በአዲስ ብራንድ መተካት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ያስረዳል፡፡

 የአዲሱ ብራንድ መዘጋጀት አስፈላጊነት

 - በአለም አቀፍ ደረጃ የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ መለያ እንዲኖረው በማድረግ ተወዳዳሪነትን ማሳደግ

 -በየትኛውም አለም ያለ ሰው ስለ ኢትዮጵያ አጠቃላይ የቱሪዝም ሀብት መረጃ እንዲያገኝ ያስችላል።

 የቱሪዝም መዳረሻዎችን፣ የዱር እንስሳት ሀብትና ሌሎች የሀገሪቱን ብዝሀ ሀብቶችን በተሟላ መልኩ ይገልፃል፡፡

 

 

 

 

 የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሀብት ለማስተዋወቅ ያለመው በየአመቱ የሚከበረው የቱሪዝም ቀን ዘንድሮም በሀገራችን ለ29 በአለም ደግሞ ለ37 ጊዜ ይከበራል፡፡

 የዘንድሮው የቱሪዝም ቀን "ቱሪዝም ለሁሉም ዓለም አቀፍ ተደራሽነትን ማረጋገጥ"በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡

 አዲሱ የኢትዮጵያ የቱሪዝም መለያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዚሁ ቀን ላይ ነግሶ የዘርፉን አገራዊ ተጠቃሚንት ለማጉላት ጉዞውን አሃዱ ብሎ ይጀምራል።

 

 አዘጋጅ፡- ሀና ግርማ